የካፋ ልጅ ቡና

ኮፊ ካፋ ብለህ አስጠራልኝ ስሜን

እባክህ ተረዳልኝ እወቅልኝ ድካሜን

በሆዴ አዝየ ብቅ ስትልልኝ ኮትኩቼና አርሜ

ለዓመታት ጠብቄ ብቅ ስል አበባህ

በጉጉት ስጠብቅ እንድለወጥ መልክህ

ደስታዬ ወሰን አጣ ቀይ ሆንክ ጎመራህ

እያንዳንዱን ቀዩን ለቅሜ አስለቅሜ

ጎንበስ ቀና ብዬ በደካማው አቅሜ

በጧት ተነስቼ አፍልቼ ጠጥቼ

ቸር አውለኝ ብዬ ለአምላኬ አመልክቼ

ተራራውን ይዤ ገበያ ወጥቼ

እመላለሳለሁኝ ዘይትና ላምባ ሽንኩርት ገዝቼ

እንዲህ እንዲህ እያልኩ አለፉ ዓመታት

አንድ ቀን ሳይደላኝ እንዲያው ስቃትት

አንተ የኔ ቡና በጎጀብ አድርገህ ጊቤን ተሻግረህ

ክፍለ ሀገሮችን ሁሉንም አዳርሰህ አፍርካን ዞረህ

ዓለምን በሙሉ በፍቅርህ ሱስ አስረህ

መኖር ጀምረሀል በጫካው በሜዳው በየጓሮ ቦቅ

ተብለህ ተጠርተሃል  አረንጓደው ወርቅ

ከእኔ ተለይተህ ሄደሃል እሩቅ

ያንተ ዝና ቢገንም ከአጥናፍ አጥናፍ

ህዝቤ አልተጠቀመም አላገኘም ትርፍ

ደፋ ቀና ብሎ የለፋው ገበሬ

ተጠቃሚ አልሆነም ከአረንጓደው ፍሬ

በጣም የሚደንቀው የሚገርመው ነገር

በጓሮዋ የሌላት አንድ የቡና እግር

ብቅ አለች ኤርትራ ከኤክስፖርተሩ መንደር

ቡና ቡና እያሉ ዘፍነው አዘፍነው

ልጄን አስኮበለሉት ባህሩን አሻግረው

አሁን አሁንማ እንደሚንሰማው በየሚዲያው

አፍርካ እስያ ላቲን አሜሪካ

ሀገራቸው ከፍተው የቡና ፋብሪካ

ኮፊ ካፌ እያሉ ቅጽል ስም ሰጥተው

ረሳ ማንነቱን ዜግነቱን ሸጠ

ድሃ እናቱን ረስቶ ስሙንም ለወጠ

ኧረተው አንተ ቡና የማንኪራ ፍሬ

ስደተኛ አትሁን ኮብልለህ ከምድሬ

ከባህር ወዲህ ማዶ እዚሁ ሀገሬ

አንድ አንድ ጎረቤቶች የሚነዙት ወሬ

ሆዴን አቆሰለው ሆንኩኝ ተናዳጅ

አንተን አደረጉህ የእኔ እንጀራ ልጅ

ቀምተው ለመውስድ ዝና ከማንኪራ

የኔ የወላጅህ ስሜ እንዳይጠራ

የአንተን ከማንኪራ መወለድ ዘንግተው

ሲሯሯጥ አያለሁ ቡና የኛ ነው ብለው

ከካፋ በስተቀር ሀገር ከተማ ሌሎችም ጭምር

ሆኑ ተጠቃሚ ከአንተ በተገኘው ዶላርና ብር

እናትህ ወላጅህ ደፋ ቀና ብዬ

አልተስተካከልም አሁንም ኑሮዬ

ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ሆነና ነገሩ

ታሪክ ቢከላለስ ቢደበቅ ምስጢሩ

ማንኪራ ካፋ ነው የቡና መንደሩ

እናንተ የካፊ ቡሾ ማህደር አገላብጡ

ታሪክ መርምራችሁ እውነቱን ግለጡ

ቀና ቀና በሉ ሁላችሁም ኩሩ

ዓለም ያውቃችኋል ማንነታችሁን እናንተ ባታወሩ።

ከፋንታዬ መኮ