ሰሞኑን በጥምቀት በዓል አከባበር እና በተከታታይ ቀናት በወልዲያ እና በሌሎች አካባቢዎች በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች በተወሰደ ህገወጥ ርምጃ ምክንያት የሰላማዊ ዜጎች ህይወት መጥፋቱን አስመልክቶ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረት የተሰጠ መግለጫ

በየትኛውም ሀገር ሃይማኖታዊም ሆኑ ባህላዊ የአደባባይ በዓላት በሰላም ይጠናቀቁ ዘንድ መንግስት ተገቢውን ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ይታወቃል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በርካታ በዓላትን ለዓመታት ሕዝብ ወደ አደባባይ በመትመም በሰላም እያከበረ ወደቤቱ ሲመለስ ኖሯል። በዓላትን ለማክበር ወደ አደባባይ የሚወጡ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ህዝቦች ለዘመናት በአምባገነን መንግስታት ይደርስባቸው የነበረውን በደል በየበዓላቱ ላይ በዜማ ሲገልፁ መቆየታቸውን ማንም የሚያውቀው እውነት ነው። ይልቁንም አንዳንዶቹ መንግስታትና ነገስታት ዜማዎቹን ጆሮ ጠቢዎቻቸውን በመላክ ህዝቡ ምን አለ? የሚለውን በማዳመጥ በከፊልም ቢሆን የአስተዳደር ዘይቤአቸውን ለማሻሻል ሲጠቀምበት ተስተውሏል።

ይሁን እንጂ በተለይ ህወሓት መራሹ መንግስት በዴሞክራሲና በእኩልነት ስም እየማለ የተቃውሞ ዜማዎችን እንኳ መታገስ አቅቶት በሀገራችን ሕዝቦች ላይ ሞት የሚያዘንብ የምፅዓት ደመና ሆኗል። በተለይም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ አገዛዙ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎች ላይ የሕዝቡን ሰላም ሊጠብቁ በሚገባቸው ወታደሮቹ አማካይነት ጥይት በመተኮስ ለበርካቶች ህይወት መቀጠፍ፣ አካል መጉደልና ኑሮ መናጋት ምክንያት ሆኗል። ቀላል ምሳሌዎች ለማንሳት ያክል ከአምስት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ እንዲሁም ከአንድ ዓመት በፊት በቢሾፍቱ ሆራ ሐይቅ አካባቢ የእምነት ሥርዓታቸው የሚፈቅደውን ለመፈፀም በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀመውን ርምጃ ማስታወሱ በቂ ነው። ከዚህ ሁሉ በኋላ በቅርቡ አገዛዙ ባለፉት ጊዜያት ለፈፀምኳቸው ስህተቶች ተፀፅቻለሁና ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችንም እፈታለሁ፤ ባለ ማግስት በወልዲያ ዓመታዊውን የጥምቀት በዓል ለማክበር በወጡ ምዕመናን ላይ ተኩስ ከፍቶ የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፍ ወደለየለት አረመኔያዊ ተግባሩ ተመልሷል። ይህ ሁሉ የጭካኔ ርምጃ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዘነ ብቻ ሳይሆን በቁጣ እንዲነሳሳ ምክንያት በመሆኑ ባሁኑ ወቅት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕዝባዊ ተቃውሞው እንደገና በማገርሸት ላይ ይገኛል። ተቃውሞንም በኃይል ለማስቆም የሚደረግ ማንኛውም ርምጃ መንግስትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ከወዲሁ ሊገነዘብ ይገባል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረት መንግስት በተከታታይ እየፈፀመ ባለው ህገወጥ ርምጃ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በሙሉ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀና ሥርዓቱን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ከህዝቡ ጋር በአጋርነት እንደሚቆም እና የሚወክለውን ህዝብ ትግል በማስተባበር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ በድጋሚ ያረጋግጣል። የሚወዷቸውን በሞት ለተነጠቁ ወገኖችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን እየተመኘ በጀመረውም ትግል በስሙ ሥልጣን ይዘው ከሚነግዱ ጨካኝ ገዢዎች መዳፍ የሚላቀቅበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን እርግጠኛ ነው።

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ!