ልብ በይ አፍሪካ

አፍሪካ ቀና በይ ንቂ ከእንቅልፍሽ

ራስሽን ቻይ መሰደድ ይብቃሽ

ሀብት ሞልቶ ተትረፍርፎ በአህጉርሽ

ብዙ ማዕድናት አምቀሽ ይዘሽ

ወርቁ አልማዙ ብሩ ታምቆ ሆድሽ

ዛፍና ቅጠሉ ቡናው ፍራፍረው ሞልቶ ከጓሮሽ

ታዲያ ምን ጎሎሽ ነው ስደት ያማረሽ

የቆጥ አውርድ ብላ ጥላ የብብትዋን

የሰው ስታሳድድ አስቀምጣ የራስዋን

ዓለም ላይ በተነች ውድ ልጆቹዋን

ያልተነካ እምቅ ሀብት ይዛ በጉያዋ

ለልጆችዋ ጥቅም ባለማዋልዋ

እየኮበለሉ ልጆችዋ ይወጣሉ

በስተመጨረሻ ውዳቂ ተባሉ

አፍሪካ አመቻች ኑሮ ለልጆችሽ

ልጆችሽን ማሳደድ መናቆሩን ትተሽ

ሀገራቸው ገብተው እንድያገለግሉሽ

ባለ ብዙ ባህል ባለብዙ እሴት ያች ታላቅ አህጉር

ምንድነው ምክንያቱ የአፍሪካ መደፈር

ምን ይል ይሆን ማንዴላ ያ ታላቁ መሪ

ይቅርታን የቸረ ለአፓርታይድ ወራሪ

ክብራችን ሲነካ በአለም በአደባባይ

እናንተ አፍሪካዊያን አይቆጫችሁም ወይ

በአድዋ በማይጨው ድል ያስመዘገበች

ለነጭ ቅኝ አገዛዝ ያልተንበረከከች

አንዷ የአፍርካ ሀገር ኢትዮጵያ ነች

ሌሎቹም ቢሆኑ የአፍርካ መንግስታት

ከቶ አልተበገሩም ለወራሪ ጠላት

ሁሉንም ጠራርገው በውርደት ሸኙት

ታፍራና ተከብራ የኖረች አህጉር

ታላቅ ነች አፍርካ ከቶ የማትበገር

የቅኝ ገዢዎች ሽንፈትን ተላብሰው ከሀገር ስለወጡ

የልጅ ልጆቻቸው ይኸውና ዛሬ ልበቀሉን መጡ

ውዳቂዎች ሊሉን በጠራራ ፀሀይ አደባባይ ወጡ

እባክሽ አፍርካ ከእንቅልፍሽ ንቂ

ወዳጅ ጠላትሽን ጥንቅቀሽ እወቂ

ሰብስቢ ልጆችሽን አስገቢ አህጉርሽ

ደሃ እኮ አይደለሸም በጣም ሀብታም ነሽ

ብለው እየጠሩሽ ዳርክ ኮንቲኔንት (Dark Continent)

ግን ይሯሯጣል ሀብትሽን በመዝረፍ ለመቀራመት

የሥልጣኔ አምድ የሰው ዘር መገኛ

ናት እኮ አፍርካ ከአለም አንደኛ

ሀሰትም እንደሆን ታርክ ይፍረደኛ።

ፋንታዬ መኮ