የሀገር ኩራት

ጦረኛ መጥቶብኝ የዛሬ መቶ ዓመት

ህዝቤን አሰልፌ ከፈለኩኝ መስዋዕት

ወገን ለመታደግ ለካፋ ነፃነት

ግን ምን ያደርጋል ጊዜ ጣለኝና

እጃቸው ገባሁኝ ታሰርኩ በካቴና

ተሸንፌ ሳይሆን በሸዋ መኳንንት

እጄ የታሰረው በወርቅ ሰንሰለት

ከራሴ ላይ ዘውዱም ቢወሰድ በጉልበት

አልተንበረከኩም ለሚኒልክ መንግሥት

እኔም አንተም ንጉሥ ማንበላለጥ

ግብር አልገብርም እጄንም አልሰጥ

ብሎ የመለሰ በኩራት በድፍረት

ጋኪ ሻረቾ ነው የካፋ ህዝብ አባት

አልበገር ያለ ለሚኒልክ ጦር

አልበገርም ያለ የቆመ ለሀገር

ከሻረቾ በቀር ሌላ ማን ነበር

ጦርነት የፈሩ የሸዋ መኳንንት

ተልከው ነበር ጋኪን ለማግባባት

የጋኪ ሻረቾን የዚያን የካፋ ጀግና

እነ ሀብተጊዮርጊስ ተጠርተው ይምጡና

ለምስክርነት ቤርቤር ይጠራና

ያውሩ ጀግንነቱን ዛሬም እንደገና

አሳልፎ ያልሰጠ የካፋን ምድር

ይኸ ታላቅ ንጉስ ይገባዋል ክብር

አፈር ቢጫነኝም ብገባ መቃብር

ዛሬም ዘብ ቆሜአለሁ ለሀገሬ ክብር

ለብዙ ዓመታት በእስር ቆይቼ

አንገቴን ሳልደፋ ጠላቴን መክቼ

የጀግንነት ዓርማ ለትውልድ ትቼ

የሀገሬ ወጣት ታዲያ ምን ነክቶህ ነው

ድካሜን ለፋቴን ከንቱ ያደረከው

ይህን ሁሉ በደል ቆመህ የምታየው

አንተ የካፋ ወጣት ዛሬ ምን ነክቶህ ነው

ሀብትህን ሲዘርፉ በቃ የማትለው

የሀብት ማነስ ነው ወይስ የእውቀት

ምንድነው መንስኤው የአንተ ድህነት?

ፋንታዬ መኮ