ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት እና ከጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የቀረበ ጥሪ

የተከበራቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በሃገራችን ላይ እየደረሠ ያለውን ጭቆናና የግፍ አገዛዝ በመቃወም በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር በመደራጀት በትግል ላይ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ። 26 ዓመታት በወያኔ መንግስት የግፍና የጭቆና ቀንበር አገዛዝ ሥር በመውደቅ ለበርካታ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች የተጋለጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃውሞውንና እንቢተኝነቱን በሃገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ማሰማት ከጀመረ ዓመታት አስቆጥሯል።  በመሆኑም የወያኔ መንግስት እየተከተለ ያለው የዘረኝነት ፖለቲካ በአንድነቷ ፀንታ የቆየችውን ኢትዮጵያን በመበታተን ህዝቡን እርስ በእርስ እንዲጋጭና ሃገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስ እያመራች በመሆኑ ምሬትና ብሶት ያንገሸገሸው የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆቹ ገሚሱ ለእስር እና ለስደት በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለነገይቱ ኢትዮጵያ ነጻነት ውድ ህይወታቸውን በመገበር ልይ እንደሚገኙ ይታወቃል። የተከበራቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከቀን ወደቀን እየበረታ የመጣውን የህዝብ ተቃውሞ ለመቀልበስና የግፍና የጭቆና አገዛዙን እድሜ ለማራዘም ወያኔ በተለያዩ ወቅቶች የማዘናጊያና የማደናገሪያ ሥልቶች ሲጠቀም እንደነበር የማይካድ ሃቅ ነው።

ስለሆነም በቅርቡ በጭንቀትና በውጥረት የተሞላው የወያኔ ኢህአደግ የ17ቀናት ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ የፖለቲካና አንድአንድ የታሰሩ ግለሰቦችን እፈታለሁ ብሎ የተምታታና እርስ በእርሱ የሚጣረዝ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። እንደሚታወቀው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች የመሰደዳቸው ፣የመታሰራቸውና የመሰዋታቸው ዋነኛ ሚስጢር በቁም እና በህሊና እስረኝነት የሚሰቃዩ የኢትዮጵያ ህዝብን ነፃ ለማውጣት እንደነበር ወያኔዎችም የሚጠፋቸው እውነታ አይመስለንም። ሆኖም የወያኔ መንግስት ከተደቀነበት ውጥረትና ከተጋረጠበት የገነፈለ የህዝብ ሥሜት ለመሸሽና ውንብድናውን አጠናክሮ ለመቀጠል የዘየደውን ከንቱ ዘዴ መላው የሃገራችን ህዝብ በጥንቃቄ እንዲመለከተውና እንደሚያጤነው እንገነዘባለን። በገዛ ሃገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ በመቆጠር ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ የመብት ረገጣ የተዳረገውና ላለፋት 26 ዓመታት በጉስቁልና ህይወቱን እየገፋ የሚገኘው ጀግናው የኢትዮጱያ ህዝብ በወያኔ የማደናገርያና የማዘናጊያ ታክቲክ ሳይታለል ትግሉን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደምገባው በአፅንኦት እንገልፃለን። ከራሳቸው ክብርና ርካሽ ጥቅም ይልቅ ለህዝባቸው ነፃነት መከበር አምርረው በመታገል ላይ የሚገኙ ብርቅዬ የገዥው ፓርቲ አባላትና አመራሮች በጀመሩት ያላሰለሰ ትግል የመላውን ህዝብ የልብ ትርታ በማዳመጥ ለላቀ ድል ወደ ፊት መገስገስ እንደሚገባቸው ለመጠቆም እንወዳለን።

 በቡድንና በፖለቲካ ድርጅት በመታቀፍ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት የኢትዮጵያን ህዝብ ከወያኔ የግፍ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በመታገል ላይ የምትገኙ ሁሉ ምንም እንኳን በአደረጃጀት ባህሪ በተለያየ መንገድ ብንደራጅም የመዳረሻ ግባችን አንድ ነውና ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ በውስጣችን ያለውን ልዩነት በማጥበብ ተቀራርበን በኢትዮጵያ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የወያኔ መንግስትም ቢሆን በመላ አገሪቱ የሚገኙ የህሊና ታሳሪ የሆኑ የፖለቲካ፣የሲቪክ ማህበራት መሪዎችንና ጋዜጠኞችን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመፍታትና ተገቢውን ካሳ በመክፈል  ሥልጣኑን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለባለቤቱ ለተከበረው ህዝብ እንዲያስረክብ እንጠይቃለን።

 በመጨረሻም የፖሊስ እና የተከበራቹ የመከላከያ ሠራዊት አባላትም እየተረገጠ እና እየተጨቆነ ያለው የወገናችሁ ብሶትና በደል ተሰምቶአችሁ እስከዛሬ ለግድያና ለድብደባ የወሰዳችሁትን የመሣሪያ አፈሙዝ ወደ ላይ በማንሣት ለህዝብ ነፃነት እየታገሉ ካሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ጎን በመቆም በወርቅ መዝገብ ላይ የማያልፍ ታሪክ እንድታስመዘግቡ በአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ለዘመናት ፀንቶ የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ዛሬም ሆነ ለወደፊት እንደተጠበቀ ይኖራል!!!