የደኢሕዴን ዝምታ ሚስጢሩ ምን ይሆን?

የህወሃት የትግል ታሪክ እንደሚያስረዳን ከሆነ የትግራይ ህዝብ የነፃነት ጥያቄ ለመመለስና ነፃ ለማውጣት ቢሆንም ወዳጆቻቸው በነበሩ ባለፈርጣማ ክንድ ሃገራት ድጋፍና ጣልቃ ገብነት በለስ ቀንቶአቸው የደርግ መንግስት (አገዛዝ) እንደተገረሰሰ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ሥልጣን ቁንጮ ላይ ሊወጣ ችሏል። ህወሃትም በትረ ሥልጣኑን ከጨበጠ ከዓመታት በኋላ በአመራሩ መካከል የተፈጠረው መፈረካከስና ቡድንተኝነት ተከትሎ የአንደኛው አንጃ አቀንቃኝ ነው ተብሎ በጥርጣሬ ቀለበት ውስጥ የገባውና በራሱ በህወሃት አምሣል የተፈጠረው የዚያኔው ደኢህዴግ የአሁኑ ደኢህዴን በወቅቱ ሥር እየሰደደ የመጣውን የህወሃት የበላይነት ሊቆም ይገባዋል ፓርቲው ከሞግዚት አስተዳደር ወጥቶ በራሱ ቁመና መመራት አለበት የሚለው ተቃውሞ መበርታቱን ተከትሎ ፓርቲውና አባላቱ መታደስ አለባቸው የሚል ሥልት ተቀይሶ ሥራ ላይ እንዲውል ተደረገ ። ይህንን ተሃድሶ በበላይነት የሚመራ እና የህወሃትን ተልዕኮ በታማኝነት የሚያስፈጽም መልዕክተኛ ሲፈለግ ደግሞ በውቅቱ የኦህዴድ አመራር የነበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ ለመድረኩ ይመጥናሉ ተብለው ተመደቡ። አቶ አባዱላም የተሰጣቸውን የሞግዚትነት ተልዕኮ ተቀብለው መላው የደኢህዴግ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ሃዋሳ ከተማ ላይ የተሃድሶ ፕሮግራም ለተከታታይ ሁለት ወራት እንዲካሄድ ተደረገ።በዚህ የግምገማ ሂደትም የህወሃት ስወር ደባ አስፈጻሚ አባዱላም ለህወሃት ያላቸውን ታማኝነት በፅናት ለማስፈፀም ከነበራቸው ቁርጠኝነት የተነሣ በግምገማው ላይ ጠንካራ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ብርቅዬና ምን አልባትም እስከዛሬ ቢቆዩ ኖሮ በአሁኑ የኢትዮጵያ የተቃውሞ አብዮት ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ይሆኑ የነበሩ በርካታ ጓዶች ሠለባ እንደሆኑና ጥቂት የማይባሉትም ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን በውቅቱ የግምገማው አካል የነበሩ ጓዶች የማይዘነጉት ሃቅ ነው። እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው የደኢህዴግ ጓዶች አንዱና ዋነኛ ትግል የነበረው በግምገማ ወቅትና ከዚያም በፊት በድርጅታዊ ድጋፍ ሥም ለስለላ ተግባር ተመድበው የነበሩ ለምሳሌም ያክል እንደ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ያሉ የህወሃት ካድሬዎች ክልሉንና መድረኩን ለቀው እንዲወጡ የሚል ግፊት በመበርታቱ እነሱም ለቀው ወጥተዋል። የደኢህዴግ እና የአባላቱ አጠቃላይ ጥንካሬና እንቢታ ያሰጋው የህወሃት መንግስት ብዙም ሳይቆይ በ1995 ዓ.ም ደግሞ ተሃድሶ እንዲካሄድ ባሳለፈው ውሳኔ ድራማዊ በሆነ መንገድ በሃሰት በተቀነባበረ የቪድዮና የጹሑፍ መረጃዎች እንዲቀርቡ ተደርጎ የህወሃት ሸፍጥ የተሞላበት የጭቆናና የግፍ አገዛዝ ያንገሸገሻቸው የቁርጥ ቀን የህዝብ ልጆች የሆኑና በጥንካሬአቸው የሚታውቁ ካድሬዎች እንዲወገዱና በምትካቸውም የህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑ ነገር ግን በተቃራኒው የክልሉን ህዝብ ጥቅም አሳልፈው የሸጡ ተላላኪዎች ሥልጣን እንዲይዙ ተደረገ። በመሆኑም አሁን በዳቦ ሥሙ ደኢህዴግ ከየትኞቹም መሠል ብሔራዊ ድርጅቶች ቀድሞ ገና በጠዋቱ የህወሃትን ጋጠወጥ የጭቆና አገዛዝ በመቃወም ለወከሉት ህዝብ ያላቸውን ታማኝነት በቁርጠኝነት የገለጹ ካድሬዎች ስብስብ የነበረው የኸው ድርጅት ምንም እንኳን በህወሃትና በተላላኪዎቹ የበረታ ክንድ ተመቶ በአንፃሩ በራሱ ሰዎች እንደገና እንዲዋቀር ቢደረግም ዛሬም ቢሆን ህዝባዊ ወግንተኝነት ያላቸው የህወሃት ግፍ አገዛዝ የመረራቸው ግን ደግሞ ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የሚያስደነግጥ ቁዘማ ውስጥ ቢሆንም በእኔ በፀሀፊው ደምሳሳ ግምት **የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይቀልድም** ወደ ሚለው ወደ አበው ብሂል ይወስደናል ብል ተሳስተሃል አልባልም። ዛሬ እንደምናስተውለው ብሶትና ምሬት የወለደው ትግል በተለይም በኦህዴድና ብአዴን አከባቢ እየገነፈለ በመጣበት ወቅት የደቡብ ክልልን በበላይነት የሚመራው ደኢህዴንና የህዝቡ ዝምታ እውነት ለመናገር ህወሃትን ተቃውመዋል። በመላው የኦሮሞ ህዝብ ላይ በህወሃት መንግስት እየደረሰ ያለው ግፍና በደል እሳቸውንም አንገሽግሾአቸዋል የተባሉት አባዱላንም ሣያስገርም አልቀረም። ስልሆነም የህወሃት መንግስት ፀረ- ዴሞክራሲያዊና ኢ- ፍታዊ ብሎም አምባገነናዊ አገዛዝ እንደሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የደቡብ ህዝብንም በእጅጉ የጎዳና ለምሬት የዳረገ እኩይ ድርጊት ስለመሆኑ የአደባባይ ሃቅ ነው። አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስተርነት የሚመሩ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝን ጨምሮ በርካታ አመራሮችና ካድሬዎች ያሉበት ደኢህዴን አብጦ ሊፈነዳ የተቃረበውን ህዝባዊ ተቃውሞ በህወሃት አመራሮችና ካድሬዎች የጀርባ ግፊት ከማፈንና ከመድፈቅ አባዜ ተላቀው በዚህ ታሪካዊ የትግል ምዕራፍ እነርሱም ተነቃቅተው መላውን ሕዝብ በማንቀሣቀስ ጨቋኙንና አምባገነናዊ ሥርዓት በቃ ሊሉት ይገባል።

ጎዲ ጃሹ godi72@yahoo.com