ከደቡብምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ኅብረት እና ከጋምቤላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ፤

እንደሚታወቀው የህወሓትኢሕዴግ መንግሥት ባለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጦ የአፈና፣ ጭቆና፣ ብዝበዛና ግድያ ቀንበሩን በመጫን የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከመርገጥ አልፎ ለዘመናት ገንብቶት የኖረውን አብሮነትና የመቻቻል ባህል በብሔር ተኮር ፖለቲካ በመተካት የዘር ጥላቻ እንዲነግሥና ሃገሪቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫና ብተና እንዲሁም ወደ ትርምስ እንድታመራ እኩይ ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል።

እኛ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጽያ  ሕዝብ ህብረት እና የጋምቤላ ሕዝብ አንድነት በጋራ በመሆን ይህንን መግለጫ እንድናወጣ የተገደድንበት ዋነኛ ምክንያት በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የሰው ልጆች በመደብ መተዳደር ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የውጭ ጠላትን በጋራ መከላከል እንጂ ተጋጭቶ የማያውቁትን የአሮሞና ሱማሌ ህዝቦች የራሱን ሠራዊት አስቁሞ እልቂ ት እያካሔደ የሚገኝ ሲሆን ይህንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትር ሃ/ማርያም ደሳለኝ የሰጡት አድሎአዊነት የተሞላበት መግለጫ አሳዝኖናል። በመሆኑም ይህ ስርዓት ካልተወገደ ሀገራችን አደገኛ መንገድ ላይ ስለምትገኝ ሁሉም እውነተኛ ሀገር ወዳድ ተቃዋሚ ሃይሎች ህዝባችንን አስተባብረን በሁለንተናዊ ትግል በአስቸኳይ በጋራ እንድንቆም እናሳስባለን።   

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት፣ ህብረትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያበሳጨውና ያንገበገበው የወያኔ ባለሥልጣናት በተለይ በምሥራቁ ኢትዮጵያ የተመደቡት ኮንትሮባንድ ነጋዴ ጀኔራሎች የኢትዮጵያን ሱማሌ ፕሬዝዳንት በግልጽ በመርዳትና በመወገን  የሚያቀነባብሩት ይፋዊ አድሎ ብቻ ሳይሆን ለሃገራችን አንድነት ቀውስ የሚፈጥር ሴራ ሁሉንም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ያሳዘነና ያስቆጣ ስለሆነ በአስቸኳይ ለማስቆም ሁላችንም በጋራ መስራት ይጠበቅብናል።

እንደሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ከሕዝብ ጥቅምና መብት መከበር  ዓላማ ላይ የተመሰረተው ድርጅታችን ይህንን አፋኝና ጨቋኝ ሥርዓት  ለመገርሰስ በሚደረገው ወሳኝ የታሪክ ትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። በመሆኑም ሃገር ወዳድና  ተራማጅ ሃይሎች ሁሉ የጀመሩት መራራና ወሳኝ ትግል ሲኬታማ የሚሆነው የተለያየ የፖለቲካ አካሄድ የሚከተሉ ነገር ግን ወደ አንድ ግብ ለመድረስ የተሰለፉ ሁሉ ልዩነታቸውን በማቻቻልና በማቀራረብ ዛሬ ሃገሪቱ ከገጠማት የብተናና የዜጎችን እልቂት መታደግ ሲቻል ብቻ ነው ብለን በጽኑ እናምናለን።

በዚህ ፈታኝ በሆነ የትግል ሂደት ውስጥ ለያንዳንዳችን ለነገ ነፃነት ውድ ሕይወታቸውን በየቀኑ መስዋዕት እያደረጉ ላሉ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ድርጅታችን ያለዉን ታላቅ አክብሮት እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው እና ትግሉን እያስቀጠሉ ላሉ የትግል አጋሮቻቸው መፅናናትን ይመኛል፤ በተለይ በቅርቡ በወያኔ ቅንብር በኦሮሞና ሱማሌ ወገኖቻችን ላይ በደረሰውና እየደረሰ ላለው እልቂትና ጉዳት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እንገልጻን።

የወያኔ መንግሥት ዕድሜውን ለማራዘም እየተከተለ ያለውን የተሳሳተ ስትራተጂ ለማክሸፍ የኦሮሞና ሱማሌ ክልል መንግሥታትና በተለይም ሕዝቡ በሰከነና በሳል አመለካከት የተፈጠረውን የዘር ጥላቻ በፍቅርና በመቻቻል እንደሚተካው እምነታችን የጸና ነው።

ስለሆም በተለይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከጊቤ መለስ ከየም እስከ ማጂ፤ ደቡብ ሕዝቦች ከሚባለው አሣፋሪና ጥገኛ አሸንጉልት የወያኔ ድርጅት ራሱን አግልሎ የማይቀረውን ለውጥ በመቀላቀል ታርክ እንድትሠሩ በጥብቅ እናሳስባለን።

በመጨረሻም በደቡብምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላንም ጨምሮ የወያኔ ሥርዓት አራማጅ  ባለሥልጣናት፣  ካድሬዎች፣  ምሁራንና በየደረጃው የምትገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች  በሙሉ!! በዚህ ወሳኝና ታሪካዊ የትግል ምዕራፍ ውስጥ ከተበደለውና ከተጨቆነው ወገናችሁ ጎን በመሰለፍ የትግሉ አካል እንድትሆኑና ከታሪክ ተወቃሽነት እራሳችሁን ነፃ እንድታወጡ በተበዳዩ ሕብረተሰባችን ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን ።

ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲና እኩልነት ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ከደቡብምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕብረትና የጋምቤላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር