ኃላፊነታችንን እንወጣ!!!

መንግስትን  የተቸ ሁሉ  በጠላትነት ሲፈረጅ እያየን ነዉ ። በየትኛዉም ህብረተሰብ መንግስት ለትችት የተጋለጠ አካል ነዉ። ምክንያቱም መንግስት የህሕዝብና የሀገር ህሌዉና ጠባቂና ፤ የበርካታ ልዩነቶችና አመለካከቶች ባህር የሆነዉን ህዝብ የሚያስተዳድር  ህዝባዊ ተቋም ነዉ። ይህንን ተቋም ይዞ ማንም ሳይናገረኝ እንዳሻኝ ላድርግ ማለት የማይቻል ሐቅ ነዉ። ባለቤት የሆነዉ ህዝብ የሚያቀርበዉን ማናኛዉንም ትችት በበጎ ጎኑ ተቀብሎ ማስተናገድ የግድ ይላል። አልያ የሕዝቡ ቁጣ የማይመከት ኃይል ስለሆነ ያልፈለገዉን መንግሥት ሆነ ባለሥልጣናትን ማስወገዱ የማይቀር መሆኑ ብዙ ምርምር ሳያስፈልግ የሀገራችንን ታሪክ ወደ ኃላ ዞር ብሎ ላየ ሰዉ በጣም ግልጽ ነዉ። እናም ትችትን  የማይቀበል  የመንግስት አካል   ለመስተካከል የማይሻ፣ የህዝቡን አደራና አመኔታ የከዳ አምባገነን ነዉ።እናም የሀሳብ ነጻነትን ይከለክላል ማለት ነዉ።ሀሳቡን በነጻነት መግለጽ ያልቻለ ህዝብ ሀሳቡን በአመጽና በታቃዉሞ  መግለጹ የማይቀር መሆኑ በታሪክ በተደጋጋሚ የተረጋገጠ በሀገራችንም ጭምር የታየ ሐቅ ነዉ። አሁን በኢትዮዽያ እየተከሰተ ያለዉ ይሄዉ ነዉ።ሀሳቡን በነጻነት መግለጽ ባለመቻሉ ህዝቡ  በህቡዕ ተደራጅቶ በአደባባይና በቤት ዉስጥ አመጽ እያደረገ ነዉ። አመጽ ደግሞ በወቅቱ በሚከሰት ተጨባጭ ክተስት የሚወሰን ስለሆነ ዉጤቱ ወዴት ሊያደርስ እንደሚችል አስቀድሞ ማወቅ ስለማይቻል አስፈሪ ነዉ። እናም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ስንል ተገቢና እዉነተኛ ትችት ልናቀርብ የግድ ይለናል።ትችቶቹ በሐቅ ላይ ያልተመሠረቱና ፍጹም የጥላቻን መንፈስ የሰነቁ ሊሆኑ አይገባም።

ትክክለኛና ግልፅ የሆኑ ግድፈቶች ለሀገር ሰላምና ደህንነት ለህዝቡ ፍትሓዊ ተጠቃሚነት ሲባል መጋለጥ አለባቸዉ። በሥልጣን ላይ ያለዉ አካልም ግድፈቶችን በማስተካከል የሀገር ሰላምና የህዝቡን ደህንነት የማስጠበቅ ሞራላዊና ሕገመንግሥታዊ ግዴታ አለበት። የሆነዉንና እየሆነ ያለዉን ክፉ ነገር፣ ሀገርን ለአደጋ የሚዳሪጉ ተግባራትን እንደ ሌብነት ወይም ሙስናን ፣ ኢፍትሓዊነት፣ አድሎ ወዘተ ያሉትን እያዩ አለመቃወምና አለማጋለጥ በማንኛዉም መመዘኛ ተገቢ አይደለም። ሀገር የባለሥልጣን ሳይሆን የመላ ህዝብ የማንነቱና የታሪኩ መገለጫ ነዉ። በመሆኑም ሀገርን ከአደጋ መጠበቅ የእያንደንዱ ዜጋ የማይታለፍ የወልና የግል  ኃላፊነት ነዉ።

ስለዚህ ኃላፊነታችንን እንወጣ!!!

ጎዲ ጃሹ