የሰሞኑ ህዳሴ ዘመቻ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ

በህዳሴ ዘመቻ ሰበብ በየዞኖቹ ገንዘብ ለማሰባሰብ  የተጠመዱ የወያኔ መንግሥት ጉዳይ አስፈጻፃሚ ካድሬዎች ሕዝቡን በማዋከብ ላይ መሆናቸው ተደምጦአል።

በመሰረቱ ሕዝቡ የተፈጥሮ ሃብቱንና በጉልበቱ ለፍቶ ያለማውን ሰፋፊ  የመንግሥትና የሕዝብ የነበሩ እርሻዎች እንደ ቡና፣ ሻይ፣ ጎማ ዛፎች እንዲሁም በጣም ለም የሆኑ መሬቶቹን እና የተፈጥሮ ጥብቅ ደኖችን፣ የከርሰ-ምድር ማዕድናት… በወያኔ ወራሪዎችና ጥገኞቻቸው ተነጥቆ ለድህንነት፣ ረሃብ፣ ለበሽታ ሲዳረግ እንዲሁም በማዳበርያ ዕዳና ግብር ጫና ቁም ሲቃዩን እያየ ባለበት ሁኔታ የወያኔ ካድሬዎች ዛሬም  የእውሸት ተስፋ እየነዙ  ሕዝቡን እያዋከቡ ይገኛሉ። በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሰበቦች የወሰዱት ገንዘብ አልበቃ ብሎአቸው ዛሬም በተገለፀው ውጥረት ውስጥ ባለበት ሁኔታ ደግሞ የህዳሴ መዋጮ እያሉ በመዝረፍ ላይ በመሆናቸው ድርጊቱን በጽኑ መቃወም ያስፈልጋል።

ለመሆኑ …

  1. በአሁኑ ወቅት ገንዘብ ማሰባሰብ ለምን አስፈለገ? 2. ህዳሴ ግድብ ለኛ እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኑ ነው? 3. ህዳሴ ግድብ እውን ልማት ወይስ ፖለቲካ?

1    በእኔ ግምገማ ገንዘብ ማሰባሰቡ ያስፈለገው የወያኔ ሥርዓት በሽብርተኛ ተዋጊነት ስም እያጨበረበረ  ከምዕራባዊያን ሃገሮች በተለይ ከአሜሪካ ያገኝ የነበረው ገንዘብ ስለተቋረጠበት ይህንን ቀዳዳ ለመሸፈን በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ግብር በመጫን ይህም በገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ባለመሳካቱ እና ቀድሞውንም በጥቅም እንጂ ለዓላማ የማያገለግለውን ካድሬ የሚከፍለውን በማጣቱ ሲሆን ፤

  1. የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በዕቅድና ጥናት የሚገነባ ቢሆን ኖሮ ባልከፋ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝብ ያልተሳተፈበትና አውንታን ያለገኘ በመሆኑ እና፤
  2. የህዳሴ ግድብ ለልማት ወይስ ለፖለቲካ ለሚለው ጥያቄ ብዙ ኢኮኖሚስቶችና በዓለም ባንክ ሳይቀር በከፍተኛ ደረጃ በሠሩት ገለልተኛ ምሁራን ግምገማ መሰረት ከልማት ይልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔና ፍላጎት እንደሆነ አስምረውበታል። እኔም ከዚህ በመነሳት ብቻ ሳይሆን ከተጨባጭ ሁኔታ በመገምገም በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ መንግሥት ባለመኖሩ ፍትሕ-እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ነፃነት ሊሰፍን ፍጹም ባልቻለበት ሁኔታ ልማት ማካሄድ ለዝርፊያ ካልሆነም የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም እንደሆነ እረዳለሁ። በመሆኑም የአባይ ግድብ ወይም የህዳሴ ግድብ  የፖለቲካ ጭንቀት የወለደው ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግ ባይሆንም የሰሜን አፍሪካ ቱኒዚያዊው ቡአዝዝ የተባለ ወጣት የአገዛዙን ሥርዓት በመቃወም ራሱን አቃጥሎ ያቀጣጠለው የለውጥ ማዕበል ወደ ኢትዮጵያ እንዳይዘምት የዜናዊ ልጅ በድንገት ከኪሱ አውጥቶ የለቀቀብን ሽፍጥ እንጂ በእውነት ለሃገር ዕድገትና ልማት ታስቦ ቢሆን ኖሮ በሸዋና ጎጃም መካከል ብቻ ከአራት በላይ የሆኑ የአባይ ገባር ትላልቅ ወንዞች ላይ ግድብ መገደብ ይቻል አልነበረምን ?  ነገር ግን በአባይ ላይ፣  ያውም ዓለምአቀፋዊ ወንዝ ላይ መገንባቱ በወንዙ ተፋሰስ ሰሜን አቅጣጫ  ያሉ ሕዝቦች ሕይወት የተመሰረተው በዚህ ወንዝ ላይ መሆኑ እየታወቀ  ግንባታ ማካሄዱ በተለይ ግብፅ  ወደ ግጭት/ጦርነት እንዲትገባና  በጦርነቱ አሳቦ  ዕድሜውን ለማራዘም የተቀየሰ ሴራ መሆኑ ያልገባው ካለ ወይም ቢኖር የሃገራችን ሕዝቦች የሃገር ፍቅር ስሜት ለመረዳት ከተፈለገ ባድሜ በተባለ ትንሽ ቦታ ላይ  ከሰባ ሺህ በላይ ወጣትና አምራች ጉልበት  ሆ!! ብሎ የወጣውን ያስጨረሰውን ሥርዓት እና የጦርነቱን ውጤት ዞር ብሎ ማስታወስና ማመዛዘን  የወያኔን እኩይ ተግባር  በትንሹ ለመረዳት አያዳግትም።  የዚህን ሥርዓት እኩይ ተግባራት ባጭሩ መዘርዘር ግፉን ማሳነስ ስለሚሆን ወደ ተነሳንበት ወደ ማጂና በዙሪያ ወዳሉበት ዞኖች እየተመመ ያለውን የህዳሴ ዋንጫ ጉዞ እንመልከት፤ ዲዚዎችና ሼኮዎች እንዲህ ይላሉ…”እን ዳዱዋ እንባብካዮ” ትርጉሙ እንዲህ ይመስላል…ኦ!!! ያባቴ አምላክ ከዚህ ጉድ አውጣኝ  ወይም ጠብቀኝ እንደማለት ነው።

ለዚህ ሥርዓት አገልግሎት የሚሰጡትን ግለሰቦችእና ቡድኖችን በሶስት ከፍሎ ማየት ተገቢ ይመስላል፤

  1. የአዲሱ ትውልድ አባል ሆኖ በወያኔ አስተዳደር ሥር ሥራውን የሚያከናውነው ወይም የሚሠራው ራሱንና ቤተሰቡን ብቻ ለመርዳት በመሆኑ ኅልናው ሥርዓቱን ስለማይቀበል እየበገነ የሚኖር እና ጊዜ የሚጠብቅ ዜጋ፤ 2. ራሱን አሳምኖና  ባርነትን ተቀብሎ የሚያገለግል ሲሆን… 3. የዘረኛ ሥርዓትን እኩይ ተግባራት በደንብ እያወቀ ፍጹም ታማኝ በመሆን የራሱን ሕዝብ ለወያኔ አሳልፎ በመስጠት እያስጨፈጨፈ ኣና እያዘረፈ  ያለው ሲሆን የዚህ ዓይነቶቹ በታሪክ ሆነ በዚህ ትውልድ የሚያስከፍላቸው ዋጋ እንደሚኖር የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው ::

በመሆኑም እኛ  በመላው ዓለም የምንኖር የአከባቢ ልጆች   ይህንን የሃገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ከሌሎች ነፃነት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ጋር መስዋሕትነት ከፍለን ከሚፈለገው ግብ  ሕዝባችንን ለማድረስ ቆርጠን መሥራት ይጠበቅብናል። ስለሆነም ካለፍላጎቱ በተጽዕኖ ብቻ ለሥራና ፍትሕ ፍለጋ አራትና አምስት ቀናት ተጉዞ ሐዋሳ በመመላለስ የሚጉላላውን ሕዝባችንን በሚመሰረትው እውነተኛ ፌደራላዊ ሥርዓት እፎይታ የሚያገኝበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ፅኑ ተስፋ አለኝ። በመጨረሻም የውሸት ዋንጫ ይዞ የሕዝባችንን ኑሮ ማራቆትና መዝረፍ ይቁም!!! ፍትህ-እኩልነት፣ ነፃነትና ዴሞክራሲ ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ብርሃኑ ወ/ ሰንበት